President Isaias Afeworki

President Isaias Afeworki

President Isaias Afeworki

President Isaias Afeworki

ፕሬዜዳንት ኢስያስ አፈወርቂ ምን አሉ ?

ትላንት ምሽት በ Eri-TV እና በድምፂ ሓፋሽ በቀጥታ በተሰራጨው የኤርትራው ፕሬዜዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቃለምልልስ ኢትዮጵያን የሚመለከት በርካታ ሀሳቦችን ሲያነሱ ተደምጠዋል።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ከ30 ዓመታት በፊት የተጠመደ ችግር ውጤት ነው ብለዋል።

በሰሜናዊ ኢትዮጵያ የተከሰተው ችግር ከዓመታት በፊት "የተጠመደ ፈንጂ መፈንዳቱ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት ከማንም በላይ እንደሚያሳስባቸው "በአካባቢው ካሉ ሌሎች አገራት በላይ ለ80 ዓመታት በችግር ውስጥ አልፈናል፤ ስለዚህም የኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት ከሌሎች በላይ ይመለከተናል" ሲሉ ነው የተደመጡት።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ የኤርትራን ሚና በተመለከተም "በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ የቻልነውን ያህል ለማበርከት እየሞከርነው" ሲሉ ቢናገሩም የአገራቸው አስተዋጽኦ በምን መልኩ እንደሆነ በግልጽ አላስቀመጡም።

ፕሬዝዳንቱ የአገራቸው ስም በተደጋጋሚ የተነሳበት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ከተካሄደው ወታደራዊ ግጭት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ በግጭቱ ውስጥ ተሳትፎ አላቸው እየተባለ ስለሚቀርብባቸው ክስ ያሉት ነገር የለም።

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት በተመለከተ፤ ለቀውሱ መነሻ የሆነውን የህወሓት ኃይሎች በማዕከላዊ መንግሥቱ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን "ፍጹም ዕብደት" ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገልጸውታል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ2 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ሠላም የማውረዱ ሂደት በተጀመረበት ጊዜ በሁለቱ አገራት የድንበር መክፈት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲታደሙ በተጠየቁ ጊዜ ፍቃደኛ ሳሆኑ ቆይተው በመጨረሻ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ በወቅቱ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩትን ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን ለማግኘትና መልዕክት ለማስተላለፍ መሄዳቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም በኦምሐጀር የድንበር መተላለፊያ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገናኝተው የቀድሞውን የትግራይ ክልል መስተዳደር "ለምን አላስፈላጊ የጦርነት ዝግጅት እንደሚያደርጉ" መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በተጨማሪ ህወሓትን አዲስ የተጀመረውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማደናቀፍ በመሞከርና የድንበር ማካለሉ እንዳይፈጸም እንቅፋት በመሆን ከሰዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያና በኤርትራ መሪዎች መካከል የተደረሰው የሠላምና የወዳጅነት ስምምነት ለአዲስ ተስፋና ሠላም ፈር የቀደደ እንደነበር የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህም ኤርትራ የድንበር ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን ከመግፋት ይልቅ ቀዳሚ ያደረገችው የሠላም ሂደቱ እንዲጠናከር ማድረግ እንደነበር ተናግረዋል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች ባልተጠበቀ ሁኔታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን የሠሜን ዕዝ ማጥቃት በተሳሳተ ቀመር ላይ የተመሰረተ የግዴለሽነት እርምጃ መሆኑን ያመለከቱት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ በዚህ እርምጃቸውም የኢትዮጵያን ፌደራል መንግሥት መጣልና በማስከተልም ኤርትራን የመውረር ዕቅድ ነበራቸው ሲሉ ከሰዋል።

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ ያለውን ብሔርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ በተመለከተም በአገሪቱ ለሚስተዋለው ፖለቲካዊ ችግሮች ምንጩ በህወሓት ተግባራዊ የሆነው ብሔር ላይ ያተኮረ ፖለቲካ መሆኑን ገልጸው፤ የአገሪቱ "ሕገ መንግስት ከመጽደቁ በፊት መለስ ዜናዊ ረቂቁን ሰጥቶኝ አንብቤ ለኢትዮጵያ እንደማይሆን ነግሬው ነበር። ነገር ግን ሊሰማኝ አልቻለም" ብለዋል።

አክለውም በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የተጠመዱና ጊዜ እየጠበቁ የሚፈነዱ ቦንቦች የሚያጠምድ በመሆኑ አገሪቱን ወደ ግጭትና መበታተን የሚወስድ ነው ሲሉ በሊቢያ፣ በየመን፣ በሶሪያና በኢራቅ የሚታዩ ችግሮችን በምሳሌ አንስተው ጎሳና የሐይማኖት ጽንፈኝነት ውጤት መሆናቸውን ተናግረዋል።

አገራቸውም ይህንን መራር ተሞክሮ በብሪታኒያ ወታደራዊ አስተዳደርና በትጥቅ ትግሉ ጅማሬ ወቅት ከነበረው ክፍፍል ትምህርት እንደወሰደችበት ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ስላለው የድንበር አለመግባባት ጉዳይ አንስተው ሁለቱ አገራት በፖለቲካዊ ሽግግር እያካሄዱ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ የሚከሰት ግጭት የህዝባቸውን ደኅንነትና ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለውና ከሱዳንና ከግብጽ ጋር መግባባት ላይ ያልተደረሰበትን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተም፤ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ለሕዝቦቻቸው የወደፊት የጋራ ተጠቃሚነት ሲሉ ሁሉንም ጉዳዮች ከግምት ባስገባ ሁኔታ አገራቱን የሚጠቅም አስቸኳይ መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በአካባቢው እየታየ ያለው ፍጥጫ የተባባሰው ፖለቲካዊ ፍላጎት ባለው የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት ምክንያት መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን በስም የጠቀሱት ወገን ግን የለም።


* ይህ ፅሁፍ ሙሉ በሙሉ የተዘጋጀው በቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት ነው።